የጄዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስላ ጽ/ቤት እና በጄዳ እና አካባቢው ከሚኖሩ የዳያስፓራ ማህበራትና አደረጃጀት አመራሮች በጋራ በመሆን ከ450 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጲያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጲያዊያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች በታደሙበት “በፍቅር እንኖራለን አንድ ሆነን እንሻገራለን” በሚል መሪ ቃል ብሔራዊ የአንድነት ቀን በቆንስላ ጽ|ቤቱ አዳራሽ በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉም በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙርና በሀይማኖት አባቶች ጸሎት የተጀመረ ሲሆን የሀይማኖት አባቶችም ሰላም ለሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን እና ሁሉም ለሰላም እጁን እንዲዘረጋ፣ አዲሱ አመት የፍቅርና የደስታ፣ የአንድነት ጊዜ እንዲሆንልን ተመኝተው ታደሚዎችም የተለያዩ የባህላዊ አልባሳት በመጎናጸፍ በሴቶች የአበባ አዮሽ ጭፈራ ደምቋል፡፡
እለቱን በማስመልከት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በጄዳ የኢፌዲሪ ቆንስል ጄኔራል አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል ˝እኛ ኢትዮጵያዊያን ትላንት ለሰላም እየሰራን የነበርን፣ ነገም ለሰላም የምናስብ እና የምንሰራ ዜጎች ነን፤ አንድነት የሁሉ ነገር መሰረት ነው፡፡ በአንድነት ውስጥ ፍቅር አለ፣ ሰላም አለ፣ መተሳሰብና መከባበር አለ፣ አንድነታችን ደግሞ የጥንካሬያችን ምንጭ ነው፡፡ በመሆኑም በፍቅር እንኖራለን በአንድነት እንሻገራለን˝ ሲሉ አዲሱ አመት የአንድነትና የስኬት ዘመን እንዲሆንልን ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም አዲሱ አመት በፍቅር ለመተሳሰርና በደስታ ለመሻገር ቃል የምንገባበት፤ አንድነታችን እና ሰላማችን በጋራ የምናጠናክርበት፤ አዲሱ አመት ተስፋችን የሚለመልምበት ደስታችን የሚፈነጥቅበት እንዲሁም ከነበሩብን ተግዳሮቶች ተላቀን ስኬታማ ስራ የምንሰራበት ዘመን እንዲሆንልን ተመኝተዋል፡፡
ከበዓሉ ታዳሚዎችም ˝እኛ በውጭ አገር የምንኖር ዜጎች በአገራችን በሚከሰቱ ግጭቶች አማካይነት የቤተሰቦቻችን ሰላም ሲናጋ አብሮነታችን ተሸርሽሮ አንዱ ሌላውን ሲጎዳ ያመናል፡፡ በሌላ በኩል አገር ሰላም ሆና አንድነታችን ተጠናክሮ ጅምር ልማቶችን ስንሰማና ስናይ ተስፋችን ይለመልማል፡፡˝ በመጨረሻም አዲሱ አመት የአገራችን ሰላም ተጠብቆ ከምንጊዜውም በላይ አድነታችን ተጠናክሮ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማየት እንደሚናፍቁ ገልጸዋል፡፡