በጅዳ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቆንስላ ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ተከበረ
17ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል በጅዳ ተከበረ፡-
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቆንስላ ጽ/ቤት 17ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን “ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል በጅዳና አከባቢዋ የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የጎረቤት ሀገራት የሚስዮን መሪዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ አክብሯል።
በዓሉ በሃይማኖት አባቶች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን የጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤት መሪ ክቡር አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል እለቱን አስመልክተው ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም “የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት አጠቃላይ መነሻ በሃገራችን ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችንን ማፋጠን፣ በሃገሪቷ የሚገኙ ሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው ዋስትና ያለው ዴሞክራሲን ማስፈን እና በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ መገንባት ነው” ብለዋል፡፡ ክቡር አምባሳደሩ አያይዘውም “ያሳለፍነው ሁለት ዓመታት አገራችን በተለያዩ መስኮች ውጤት ያስመዘገበችበት ዓመት ቢሆንም የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎችም ገጥመዋታል፤ ከእነዚህም ፈታኝ ሁኔታዎች መካከል በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተው ጦርነትና ያስከተለው አጠቃላይ ጉዳት የአገራችንን ገጽታ በማጠልሸት እና ለተለያዩ አላስፈላጊ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነትና ጫና መዳረጉ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው” ብለዋል።
በበዓሉ ላይ የተለያዩ የኮሚዩኒቲና የተለያዩ አደረጃጀት አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በጅዳና አከባቢዋ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ (ኮሚዩኒቲን) በመወከል መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ጀማል ዳዲ ኢትዮጵያውያን ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው እና ለቤተሰቦቻቸው ከሚልኩት የሪሚታንስ ገንዘብ ጎን ለጎን ለሀገራቸው ሰላም እና አንድነት ማሰብ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በበዓሉ ላይ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የየራሳቸውን የባህል አልባሳት በመልበስና የባህል ምግቦችና መጠጦች ያቀረቡ ሲሆን በጄዳ የኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ት/ቤት ተማሪዎችም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጭፈራና ዜማዎችን በማቅረብ ለመድረኩ ድምቀት ሰጥተዋል።
5