የኢትዮጵያ ባህል ቀን ጄዳ በሚገኘው የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ት/ቤት በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።
*
በጄዳ የኢትዮጵያ ባህል ቀን ዝግጅት በጄዳ የኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራል ተወካይ፣ የት/ቤቱ የቦርድ አመራሮች፣ ወላጆችና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በተገኙበት ተከብሮ ውሏል። በኢትዮጵያ አለም አቀፍ ት/ቤት የባህል ቀን መርሃ ግብር ላይ የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አብዶ አባፎጊ ለበዓሉ ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። አቶ አብዶ የት/ቤቱ ማህበረሰብ የባህል ቀንን ሲያከብር የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦችን እንዲሁም በት/ቤቱ በመማር ላይ የሚገኙ የሌላ ሀገር ዜጎች ባህልን ለማክበርና እዉቅና ለመስጠት በማሰብ የሚዘጋጅ ክብረ በዓል በመሆኑ ለዕለቱ እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ ተናግረዋል።
በበዓሉ ላይ የታደሙት በጄዳ የኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራል ተወካይ አቶ ናሆም አስራት ባደረጉት ንግግር ሀገራችን የብዝሃ-ማንነት ባለቤት መሆኗን ጠቁመዉ ለዘመናት አብሮ የዘለቀዉን የህዝቦች አንድነት አኩሪ እሴት ለመጪዉ ትዉልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ለዚህም የዚህን መሰል ክብረ በዓላት ዓብይ ፋይዳ ስለሚኖራቸዉ ተጠናክረዉ ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር አስተዋፅኦ ለበረከቱት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን በቆንስላ ጽ/ቤቱና እና በራሳቸው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በዕለቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎችን ውብ ባህል የሚያሳዩ የብሔር ብሔርሰቦችና ህዝቦች አልባሳትና መዋቢያዎች አጊጠው ተማሪዎች ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት ውዝዋዜዎች ግጥምና ድራማ አቅርበዋል።